ጾም

አንደበት ይጹም ዓይን ይጹም ጆሮ ይጹም

ጾም እስከ ስንት ሰዓት ነው?

እንኳን በሰላም አደረሳችሁ!
የቅድስቲቱ ቤተክርስቲያን ሥርዓቱ በልኬት እና በምክንያት የታጀበ ነው። ጾምን ስንመለከት አብዛኞቻችን በተለምዶ ሰዓት ሳንጠብቅ (እስከ 3፣ 6፣ 7፣ 9፣ 11 ሰዓታት እያልን) እንጾማለን እንጂ የአዋጅ አጽዋማት የተወሰነ የተገደበ ሰዓት አላቸው።

ፍትሐ ነገሥታችን “ሕማማት እስከ 12 ሰዓት ይጹሟቸው፥ ሌሎቹን አጽዋማት በዓለ ልደት እና ጥምቀት ረቡዕ እና ዐርብ የሚውሉባቸው ካልሆኑ በቀር እስከ 9 ሰዓት ይጹሙ” (ፍት.ነገ አን 15፥565-566)  ብሏል።

የአጽዋማትን ዝርዝር ካስቀመጠ በኋላም በዚሁ  አንቀጽ ቁጥር 572 ላይ ደግሞ “በእነዚህ በታዘዙት ጾሞች ከቀኑ እስከ ዘጠኝ ሰዓት ድረስ ይጹሙ፣ … ከዚህ አብልጦ  የጾመ ግን ዋጋው ይበዛለታል፣ ከጥሉላት ምግቦች መታቀብ ካልሆነ በቀር እሑድና ቅዳሜ ግን አይጹሙ” ብሎ ወስኗል።

ዐቢይ ጾም ሁዳዴ፣ ጾመ ዐርብዓ ግን ይለያል። “በዐቢይ ጾም መጀመሪያ  ሱባኤ ፀሐይ እስኪገባ ይጹሙ፣  ሌሎቹን ሳምንታት እስከ  11 ሰዓት ይጹሙ፥ በሰሙነ ሕማማት ግን ኮከብ እስኪወጣ ይጹሙ” ብለዋል። (ፍት.ነገ.አን 15፥595)።

ፍትሐ ነገሥት ቁጥር 578 ላይ ደግሞ “(የሰሙነ ሕማማትን) ዓርብንና ቅዳሜን ግን ሁለቱንም በአንድነት ይጹሟቸው፣ የሚችል እስከ ሌሊት ዶሮ ጩኸት ድረስ ምንም ምን አይቅመስባቸው፣ ሁለቱን በአንድነት መጾም የማይቻለው ግን ቅዳሜን ይጹም” ተብሎ ህግ ተሠርቷል።

በዐቢይ ጾም የተከለከሉ

(ለሚጠጡ፣ ለሴቶች፣ ላገቡ፣ ለወለዱ፣ ለካህናት)

የአጽዋማትን ሱታፌ አስመልክቶ የተከለከሉ ነገሮች አሉ። የሚከተሉትን እንመልከት።

👉 “በዐቢይ ጾም ሰርግ ማድረግም አይገባም፣
👉 ሰውን ወደ መጠጥ ቤት መጥራትም አይገባም፣
👉 ሰው ሁሉ ከሚስቱ ጋር አይተኛ” በማለትም መጠጥ እና የባልና ሚስት ሩካቤም ተከልክሏል። (ፍት.ነገ አን 15፥592 – 593)

በተጨማሪም “በዓቢይ ጾም አያጊጡ፣ ሴቶች ጌጣቸውን ይተው፣ ሁሉም ለእያንዳንዱ በጾመ ዐርብዓ እና በሰሙነ ሕማማት መጠበቅ ይቀባዋል፣ በምንጣፍ የሚገናኙ ሰዎች ከጋብቻ ህግ የወጣ ነው፣ ክብርት በምትሆን በሰሙነ ሕማማት ይህቺን ኃጢአት የሚሠራት ወዮለት!” ብሎ ጌጥን ከልክሎ ሩካቤን በሰሙነ ሕማማት ይበልጥ መከልከሉት «ወዮለት» በሚል ቃል ጠበቅ ያደርገዋል። (ፍት.ነገ አን 15፥597)

እንደገናም “በሰሙነ ሕማማት ክርስትና ማንሳት፣ ክህነት መስጠት፣ ለሞቱ ሰዎች መጸለይ አይገባም፣ በእነዚህ ቀናት ለሚሞቱ ሰዎች ግንዘትና ፍታት በሆሣዕና በዓል ቀን ይነበብ እንጂ” (ፍት.ነገ አን 15፥600) ካለ በኋላ ቁጥር 601 ላይ “በዓርባው ቀናትም ደስታ ማድረግ መጋባት ክህነት መሾም ክርስትና ማንሳት አይገባም፤ ይሞታል ተብሎ ለሚያስፈራው ግን ጥምቀተ ክርስትና ይደረግለታል” በማለት ልዩ ምክንያትን (Exception) ብቻ ክርስትና ለማንሳት በመፍቀድ አዝዘዋል።

“በዐቢይ ጾም የሰማእታት በዓል ልናከብር አይገባም፣ የሰማእታት መታሰቢያ በእሑድ በቅዳሜ ይሁን እንጂ” (ፍት.ነገ አን 15፥591) በማለት የንግሥ ክብረ በዓላት በተለይ ከሰንበት ውጪ ባሉት ዕለታት ተከልክለዋል።

ጾም ላይ ብቻ ሳይሆን ትንሳኤንም ጨምሮ “በዕለተ እሑድ የትንሳኤ ዕለት ግንዘት ማድረግ በፋሲካ ቀንም ማልቀስ አይገባም” (ፍት.ነገ አን 15፥601) በማለት ይከለክላል።

“ዓቢይ ጾምንና እሮብንና አርብን የማይጾም ሰው ካህን ከሆነ  ይሻር ምእመን /ሕዝብ/ ቢሆን ይለይ” የሚልም ለውግዘት የሚያበቃም ህግ አለ። (ፍት.ነገ.አን 15፥589)

በተቃራኒው ከካህናት ወገን የማይገባ ጾም የጾመም የተከለከለ መሆኑን  “ከስዑር ቅዳሜ ዉጪ ሰንበታን የጾመና በሰሙነ ሕማማት ቀንና ሌሊቱን ሳያስተካክል የቀኑን ሥርዓት አስቀድሞ ቢያውል ከክህነቱ ይሻር”  ተብሏል። (ፍት.ነገ.አን 15፥590) ለምመን ደግሞ ቀኖና የሚያስፈልገው መሆኑ ነው።

(ከሞዐ ተዋሕዶ ልጆች ገፅ የተወሰደ)

Leave a Reply

Your email address will not be published. Required fields are marked *